በዚህ ዕለት ጌታችን ሁለት ታላላቅ ነገሮችን አከናውኗል።
፩-የመጀመሪያው አንጽሆተ ቤተመቅደስ ይባላል
“ወቦአ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ቤተ መቅደስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ ፣ወሰደደ ኵሎ እለ ይሰይጡ ወይሳየጡ ውስተ ቤተመቅደስ ፣የሚሸጡ የሚለውጡትን ሁሉ አስወጣ ማለትም ገበያውን ፈታ። ወገፍትዓ ማዕዳቲሆሙ ለመወልጣን ፣ወርቅና ብር የሚለውጡትን ሥፍራ ውን አፈረሰ። ርግብ የሚሸጡትንም ወንበራቸውን ገለበጠ፣ ርግብ በኦሪት ለኃጢአትና ለበደል ለመስዋዕት በመቅደስ ይሰዋ ነበረና ከዚህ በኋላ መስዋዕት እኔ ነኝ ሲል፣ የመድኃኔዓለም ሥጋና ደም እንጅ የእንስሳት ደም በመቅደሱ አይፈስምና ወንበር የተባለ የኦሪት ካህናትን ሥልጣን ሻረ፣ የሐዲስ ኪዳን መስዋዕትን የሚያቀርቡ ካህናትን ሐዋርያትን ይሾማልና። ወይቤሎሙ ጽሑፍ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ(ኢሳ ፶፮፣፯ ;ኤር ፯፣፲፩) ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የሌባ ዋሻ የወንበዴም ጋሻ አደረጋችሁት፣ ገበያ ከሆነ የተቀማውን የተሰረቀውን ይሸጡበታልና ይህን አለ።
፪-መርገመ በለስ ይባላል
========≠===≠==
ወጸቢሖ እግዚእ ኢየሱስ እንዘ የዓርግ ሀገረ ርኅበ፣ማለዳ ወደ ከተማ ሲወጣ ተራበ። ወርእየ ዕፀ በለስ በፍኖት፣ በመንገድ ዕፀ በለስን አየ ፍሬ ባገኝባት ብሎ ወደ እሷ ሄደ ወአልቦ ዘረከበ ውስቴታ ዘእንበለ ቈጽል ባሕቲቱ፣ ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ አላገኘባትም ። ከእንግዲህ ወዲህ የዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት ፣ያን ጊዜ ፈጥና አንድም በምትለመልምበት ወራት ደረቀች።
ወቅቱ ክረምት ነው ፍሬ እንደሌለው ያውቅ የለም ወይ እንዴት ፍሬ ፍለጋ ሄደ ቢሉ አላዋቂ ሥጋን እንደተዋሃደ ለማጠየቅ አንድም አውቃለሁ ብሎ ሥራውንም አይተውምና በዚያው ሥራውን ለመሥራት ።
አንድም ሰው ሆኖ ሲያስተምር ከሰው ፍቅር ተራበ ዕፀ በለስ የተባሉ እስራኤልን በኢየሩሳሌም አገኘ፣ ሃይማኖት ከምግባር ባገኝባቸው ብሎ ሄደ። እስራኤል ከመባል በቀር ምግባርና ሃይማኖት ግን አልተገኘባቸውም ። ደግ ሰው አይውጣብሽ ብሎ ረገማት።ምነው እስጢፋኖስ ጳውሎስ ኤጲፋንዮስ ዓሥራ ዓራት እልፍ ካራት ሺህ ሰማዕታት የተገኙ ከእስራኤል አይደለምን ቢሉ ከእነሱ በስተቀር ደግ ሰው ጠፍቷልና።
አንድም በለስ ቅጠሉ ሰፋፊ እንደሆነ ኦሪትን በዚህ አለም ስፍና አገኛት ፣ ፍጻሜ ሕግ ተብላ ነበረ ነገር ግን ፈጻሜ ሕግ ከመባል በቀር ደኅንነትን አላደረገባትም ፣ ባንቺ ፍጹም ደህንነት አይደረግም አላት ፣ኦሪትም ፈጥና አለፈች።
አንድም ኃጢአትን በዚህ አለም ለ፭ሺህ ፭መቶ ዘመን ሰፍና አገኛት ፣ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚሽር ነውና ደመሰሳት አጠፋት ረገማት ፣ ጥንተ አብስሶንም አስወገዳት ፈጥናም አለፈች።
አንድም በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ይኮመጥጣል ፣ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ያሰኛል ኋላ ያሳዝናልና።
ወሖረ ኅቤሃ ኅጥእ ተባለ፣ ጌታም ኅጥእ ከመባል በቀር እርሱ ግን ኃጢአትን አልሰራም ነውር ነቀፋ አልተገኘበትም
ንጹሃ ባሕርይ ነውና።
ኃጢአት ንም ካንቺ በመጣ ፍዳ የሚያዝ ማንም አይኑር ብሎ በአንጻረ በለስ ረገማት ፈጥናም ደረቀች።
ሐዋርያትም በምትለመልምበት ወራት ፈጥና እንዴት ደረቀች ብለው አደነቁ። ጌታም እምነት ቢኖራችሁ ሃይማኖትን ከምግባር ብታስተባብሩ አይደለም በለስን ማድረቅ ተራራ ፣ተራራ የተባለ ዲያብሎስን ከዚህ ተነስ ወደ ባሕር ግባ ብትሉት ይደረግላችኋል።
እኛም ሃይማኖታችን ብናጸና ምግባራችን ብናቀና በሕይወታችን የሚፈታተነንን ጠላት እናሸንፋለን።
ሥርዓተ ሰሞነ ህማማት
===============
በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ምክንያቱም የደረሰበትን መከራ ኀዘኑንና ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ሕይወት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡
ከሁሉም በፊት የሰዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል: የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን፤ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር /መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፤ ድጓው ከዐራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋር እንዲስማማ ሆኖ ነው የሚቃኘው ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ የድጓው መሪ መምህር ሰኞ በቀኝ ከሆነ ማክሰኞ በግራ በኩል ባለው መምህር ይመራል እንዲህ እየተዘዋወረ ይሰነብታል ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡-
ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ኦ እግዚእየ ኢየ ሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፣
ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኮቴት
እየተባለ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ 12 ጊዜ ማለት ነው በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡ ከዚያ በመቀጠል፡-
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩ ናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ፣ /በዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ]
እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ የጀምራል፡፡ በመጨረሻ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ ምእመናንም አቤቱ ይቅር በለን እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡ ከዚያም ሁለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል፡፡ ዜማው የሚጀመረው አሁንም በቀኝ በግራ በመቀባበል ነው፡፡ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል እንዲህ በማለት:-
ኪርያላይሶን /5 ጊዜ/ በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን /2 ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን
እየተባለ በዚሁ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻም በግራ በቀኝ በማስተዛዘል አርባ አንድ ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የጌታችን ኀቡዓት ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡ በመቀጠል መልክአ ሕማማት በሊቃውንቱ ይዜማል ከዚያም ካህኑ ፍትሐት ዘወልድ፣ ጸሎተ ቡራኬ፣ ወዕቀቦሙ፣ ኦ ሥሉስ ቅዱስ፣ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፣ ነዋ በግዑ የተሰኙ ምንባባትን እያፈራረቁ ያነባሉ፡፡ ካህኑም በጸሎታቸው ፍጻሜ 41 ኪርያላይሶን በሉ ብለው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሕዝቡም መልእክቱን ተቀብሎ ይጸልያል፡፡ ዲያቆኑም ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ፤ ንዑ ወተጋብኡ ውስተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ብሎ ያስናብታል፡፡
አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነግህ /በጥዋት/ የሚከናወነውን ነው፡፡ በ3፣ በ6፣ በ9፣ በ11 ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው፡፡ የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ እዝል ነው፡፡ አሁን በተመለከትነው መሠረት ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኀን ሥርዓታቸው ይፈጸማል፡፡