ሰሞነ ህማማት # ዓርብ

በስመ ስላሴ

ዕለተ ዓርብ፡-
የስቅለት; ቀን ስቅለት፣ መስቀል፣ መሰቀል፣ አሰቃቀል ማለት ነው፡፡ መስቀል በቁሙ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መሰቀያ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ በማር 8፤34 ወጸውዖሙ ለሕዝብ ምስለ አርዳኢሁ ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ይጽልአ ለነፍሱ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀል ሞቱ ወይትልወኒ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡፡ ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ ይላል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ. 1፤17 ላይ ወኢኮነ በጥበበ ነገር ከመ ኢንስዐር መስቀሎ ለክርስቶስ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም ይላል፡፡

ጌታችን በተሰቀለ ዕለት ከሰድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ /ፀሐይ ጨለመ/፣ እነሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተውም ከነበሩት ቅዱሳን ብዙዎች ተነሱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ለብዙዎች ታዩ፡፡ /ማቴ. 27፤51/

ጌታችን ለዓለሙ ያሰበውን ቤዛነት ሊፈጽም በመስቀል ላይ መሰቀሉ የሚታሰብበት ነውና ለስቀለቱ መታሰቢያ የሚሆን አጎበር ተዘጋጅቶ ከርቤ እየታጠነ ስቅለቱ የሚመለከቱ ምንባባት ሲነበብና ሲሰገድ ይዋላል፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ በእግረ አጋንንት ረግጦ ከፈጣሪው ተጣልቶ ለ5500 ዘመን በጨለማ መኖሩን ለማስታወስም መንበሩ ታቦቱ በዚህ ቀን በጥቁር ልብስ ይሸፈናሉ፡፡ ዲያቆኑም በቤተ ክርስቲያን በመዞር የሚያሰማው የቃጭል ድምፅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅሶ አንድም ዋይ ዋይ እያሉ የተከተሉት የኢየሩሳሌም ሴቶችን ሙሾም ምሳሌ ነው፡፡ /ሉቃ. 23፤31/

በዕለተ ዓርብ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን፣ ርስተ መንግስተ ሰማያት ተመለሰችልን፤ አባታችን አዳምም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃዶ እያልን የተድላ፣ የደስታ ምልክት ወይም መገለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቆጽለ ሆሣዕና ወይም ቄጤማ ግጫ ይዘን የምሥራች እንባባላለን፡፡ /ኤፌ. 2፤14-15/ ወዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናግሮሙ፣ ያለ ምሳሌ አልተናገረምና እንዳለ /ማቴ 13፤34-35/ በኖኅ ጊዜም ርግብ ሐጸ ማየ አይኅ፣ ነትገ ማየ አይኅ፣ የጥፋት ውኃ ጎደለ፣ አለቀ እያለች ቈጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ለኖኅ አብስራዋለች፡፡ /ዘፍ. 8፤8-11/

ርግብ የካህናት፣ ኖኅ የምእመናን፣ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ርግብን እንደተቀበላት ካህናትም በየመንደሩ እየዞሩ ክርስቶስ ተመረመረ ዲያብሎስ ታሰረ በማለት ቄጤማ ሲያድሉ ምእመናንም እጃቸውን ዘርግተው መቀበላቸው የዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢገኝ የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየታደልን የምሥራች መባባላችን ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይህን ቈጽለ ልምላሜ ይዞ ተድላ፣ ደስታ መግለጽ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ከበጎ እንጨት ፍሬን የሰሌንና የተምር ዛፍ ልምላሜ ይዛችሁ በየዓመቱ ሰባት ቀን ተድላ፣ ደስታ ታደርጋላችሁ ብሏል፡፡ /ዘሌ. 23፤40-44/

በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገው ትውፊት የሐዋ. ሥራ 1፤3
ከሆሣዕና እስከ ቀዳም ሥዑር ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ናቸው፡፡ ፡፡ ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ በዚህ ሣምንት ውስጥ ለሚሞቱ ምእመናን እግዚኦ ሕያዋን ይደገማልና፡፡ በሰሙነ ሕማማት መስቀል የለም፡፡ ሣምንቱ የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ስለሆነ እርስ በእርስ መሳሳም፣ ሰላም መባባልና መልክዐ መልክዕ መድገም የለም፡፡ ይኸውም ይሁዳ ክርስቶስን በሰላምታ ስላስያዘው እርሱን ላለመምሰል፡፡ /ማቴ. 26/

በዚህ ሳምንት ብሉያትና ሐዲሳት መጻሕፍት ከጠዋት እስከ ማታ ይነበባሉ፡፡ የአምልኮ ስግደት ይሰገዳል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል መስቀልን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበትን፣ ይልቁንም ሥርዓተ ስግደትን ራሱ ሰግዶ እኛን ያስተማረንን በማሰብ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤41-45፣ ዮሐ. 4፤22-24/

ስለዚህም በዚህ ሳምንት ወርኃዊ፣ ዓመታዊ በዓል ቢሆን እንኳ ስግደት አይቋረጥም፡፡ የአምልኮ ስግደት ሳምንት ስለሆነ፡፡ ዲያቆኑ ጥቁር ለብሶ መስቀል ይዞ ቃጭል እያቃጨለ ቤተ ክርስቲያንን ሦስት ጊዜ መዞሩ ዲያቆኑ የዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ ቃጭል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆኑ፤ ዮሐንስና እመቤታችን ጌታችን የተሰቀለበትን እግረ መስቀሉን እየዞሩ አልቅሰው ነበርና፡፡

በዕለተ ዓርብ ሠርክ ሲሆን ምእመናን ወደ ቄሱ እየቀረቡ ስግደት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ቀን ሲሰግዱ ከዋሉት ሌላ ስግደት ይሰጣቸዋል፡፡ ጥብጠባ የጌታችን ግርፋት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም የተግሣፅ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ. 26፤27/

አክፍሎት
አክፍሎት ማለት ማካፈል፣ ማጠፍ፣ መደረብ፣ ሁለቱን ቀን አንድ አድርጎ መጾም፣ ጌታ ከተያዘበት እስከተነሣበት ድረስ ይህ ሥርዓት የመጣው በቤተ ክርስቲያናችን ልማድ እመቤታችን፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህልና ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ በመቆየታቸው ምክንያት ነው፡፡ በሀገራችን ብዙ ሰዎች ሐሙስ ማታ የቀመሱ እሑድ የትንሣኤ ዕለት ብቻ እህልና ውኃ የሚቀምሱት፤ ያልተቻላቸው ግን ዓርብ ማታ የቀመሱ እስከ ትንሣኤ ይሰነብታሉ፡፡ የሁለት ቀን ማክፈሉ እንኳ ቢከብድ ቅዳሜን ማክፈል ሥርዓት ነው፡፡ ቅዳሴው በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስና መቁረብ እንዳይሆን።

ወስብሀት ለእግዚአብሄር!!!